«የኢትዮጵያና የኤርትራን ሁኔታ መቀየር ይቻላል ብዬ አምናለሁ» - ሌተናል ጀኔራል ገብረፃድቃን ገብረተንሳይ የቀድሞ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም
31 May 2017
ሌተናል
ጀኔራል ገብረፃድቃን ገብረተንሳይ ለቤተሰቦቻቸው ስድስተኛ ልጅ ናቸው። በትውልድ አካባቢያቸው በራያ አዘቦ እና
በመቀሌ ከተማ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም እስካቋረጡበት 1968 ዓ.ም ድረስ ለሁለት ዓመታት ተምረዋል። የትጥቅ ትግል ከተቀላቀሉ በኋላም ከ15 ዓመታት በላይ በትግል ውስጥ ቆይተው፤ አዲስ አበባን ነጻ ለማውጣት የተደረገውን ዘመቻ እየመሩ አዲስ አበባ ገብተዋል።
ከትግሉም
በኋላ በየደረጃው የተሰጣቸውን ሀላፊነት በመወጣት፣ሙሉ በሙሉ ከድርጅቱ ተሰናብተው በመከላከያ ሠራዊት እስኪመደቡ
ድረስም በተለያዩ ሃላፊነቶች አገራቸውን አገልግለዋል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም በመሆን
ለአገራቸው ግልጋሎት ሰጥተዋል። ከመንግሥት ሥራ ከተሰናበቱ በኋላም ወደ አሜሪካ በመሄድ በጆርጅ ዋሽንግተን
ዩኒቨርሲቲ ዓለም አቀፍ ግንኙነትና በጸጥታ ጉዳይ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ሠርተዋል። ከዚያ በኋላ የደቡብ ሱዳን የጸጥታ
ሀይል አማካሪ ሆነው ስምንት ዓመት ሰርተዋል። በአሁኑ ወቅት በግል ሥራ ይተዳደራሉ። የ62 ዓመቱን ጎልማሳ ሌተናል ጀኔራል ገብረፃድቃን ስለ ኢትዮ-ኤርትራ እና ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች አነጋግረናቸው ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተውናል፤ ከእርሳቸው ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስም ለአንባቢ በሚያመች መልኩ እንዲህ አቅርበነዋል፤ መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን፡- በኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይና አገራዊ ደህንነት ፖሊሲው ላይ ያለዎት አስተያየት ምንድን ነው?
ሌተናል ጀነራል ገብረፃድቃን፡- የውጭ
ጉዳይና የደህንነት ፖሊሲ ቁምነገር እንዲኖረው አወጣጡ፣ ይዘቱና አስተዳደሩ መስተካከል አለባቸው የሚል እምነት
አለኝ። ያን ጊዜ የኢትዮጵያና የኤርትራ ጦርነት ከመጀመሩ በፊት አገራችን የምትመራበት የውጭና የደህንነት ጉዳይ
ፖሊሲና ስልት መዘጋጀት እንዳለበት በአንዳን ዶቻችን ይነሳ ነበር። ለሰባት ዓመታት ቢነሳም አንድ መቋጫ ላይ
ሳይደርስ ነው የኤርትራ ጦርነት የተጀመረው። የኤርትራ ጦርነት ካለቀ በኋላ የአገራችን የውጭ ጉዳይና የአገራዊ
የደህነነት ፖሊሲ ወጥቷል። ፖሊሲው መውጣቱ እንደጥሩ ጅምር ተደርጎ ሊታይ የሚችል ነው። ፖሊሲው የሚያስቀምጣቸው
ነገሮች አሉ።
አዲስ ዘመን፡- እንደ ጥሩ ጅምር ሊያስብለው የሚያስችለው ምንድን ነው?
ሌተናል ጀኔራል ገብረፃድቃን፡- ፖሊሲው
ዋነኛ ሥራችን አገራችን ውስጥ ያለውን ኋላ ቀርነትና ድህነትን መታገልና ማስወገድ መሆኑን ያስቀምጣል። ከጎረቤት
አገሮች ጋር በሰላምና ተከባብሮ መኖር ዋና አቅጣጫ አድርጎል። እያንዳንዱን የጎረቤት አገርንም እየጠቀሰ ምን አይነት
ግንኙነት ሊኖረን እንደሚችል ያመላክታል። በአስተሳሰብ ደረጃ የአገር ደህንነት በፖሊሲ መመራት እንዳለበትና ይህን
መነሻ አድርጎ በአገሮች መካከል ግንኙነት እንዲኖር መጣር እንደሚገባ ማስቀመጡ ትክክለኛ አቅጣጫ ነው ብዬ አስባለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ታዲያ ጉድለቱ የሚሉት ምንድን ነው?
ሌተናል ጀነራል ገብረፃድቃን፡- የውጪ
ጉዳይና የደህንነት ፖሊሲ ቁምነገር እንዲኖረው አወጣጡ፣ ይዘቱና ማኔጅመንቱ መስተካከል አለባቸው የሚል እምነት
አለኝ።እኔ በይበልጥ መናገር የምፈልገው ስለያን ጊዜው አይደለም። ያኔ ሁላችንም ሀሳብ ነበረን። በዚያን ወቅት ይህን
መከተል ነበረበት። ነገር ግን ይህን አልተከተለም። ከሁሉም በላይ ግን አሁን ፖሊሲያችንን እንከልሳለን እየተባለ
ስለሆነ አካሄዱ ይህን መከተል አለበት።
አዲስ ዘመን፡- ፖሊሲው ሲከለስ ምን ምን ነገሮችን ታሳቢ ማድረግና አካሄዱ ምን መሆን አለበት ይላሉ?
ሌተናል ጀነራል ገብረፃድቃን፡- በእኔ
አመለካከት የአንድ አገር የውጭ ጉዳይና የደህንነት ፖሊሲ ከህገ መንግሥቱ ቀጥሎ የሚመጣ የፖሊሲዎች ቁንጮ ነው።
ምክንያቱም አገር የሚመራበትን የኢኮኖሚ፣ የብሔራዊ ደህነነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ዋና መነሻ ነው። በህገ መንግሥቱ
የተቀመጡ አገሪቱ ልትደርስባቸው የምትፈልጋቸውን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚው ግቦች ለማሳካት መነሻ ተደርጎ ነው የሚወጣው።
ፖሊሲው
ሲወጣ በጣም አሳታፊ መሆን አለበት። አሳታፊ ስል በሙያው ላይ የተለያየ ዕውቀት ያላቸው ሀሳብ ሊሰጡ የሚችሉ
የፖሊሲውን ጥልቀትና ስፋት በሚፈለገው ደረጃ ሊያዳብሩ የሚችሉ የህብረተሰብ ክፍሎችና ግለሰቦች መሳተፍ አለባቸው።
እንዲህ አይነት ሰነድ የቱንም አይነት ችሎታ ቢኖርም በጥቂት ግለሰቦች ሊሥራ አይችልም። ስለሆነም ሰፊ ተሳትፎ
ያስፈልጋል።
ፖሊሲውን ከወቅቱ ሁኔታ ጋር አጣጥሞ መከለስ ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ከወቅቱ ሁኔታ ጋር አብሮ እየሄደ ነወይ? ያላየናቸው ነገሮች አሉ ወይ? ለተለዩት ችግሮችስ በቂ መልስ እየሰጠን ነወይ? የሚሉ
ጥያቄዎችን የሚመለስ አንድ ቋሚ አካል መኖር አለበት። አንድ ችግር ሲነሳ የተወሰነ ኮሚቴ ተሰባስቦ ምን ሀሳብ
አላችሁ የሚባል ሳይሆን በቋሚነት ይህን ጉዳይ መተንተን፣ ማየት፣ ተጨማሪ ሀሳቦችን ማቅረብና የሚሻሻሉ ነገሮችን
ማሻሻል ሥራው የሆነ አካል እንዲሁም በፓርላማው ውስጥም ይህን የሚከታተል መኖር አለበት።
እንደ
አገራችን በመሰለና ሰፊ የጸጥታ ችግር በሚነሳበት አገር በጣም የተደራጀ የጸጥታ አካላትን የሚመራ አካል ከሌለና
የሚመራውም በእውቀትና በምርምር በቋሚነት ሀሳቦችን እያነሳና እየተነተነ ወዴት ሊያመሩ ይችላሉ? ምን ችግር ይፈጥራሉ? እያለ በማንሳት አማራጭ የውሳኔ ሀሳብ ማቅረብ አለበት። ይህ ካልሆነ አገራችን ውስጥ ችግር ይመጣል።
ከዚህ
አንፃር ሲመዘን ፖሊሲው ሲወጣ በሚፈለገው ደረጃ አሳታፊ አልነበረም። እንደዚህ አይነት ፖሊሲ የአንድ ፓርቲ ፖሊሲ
አይደለም። የአገር ፖሊሲ ነው። የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ኢኮኖሚስቶች፣ የታሪክ
ተመራማሪዎች፣ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችም ሊሳተፉበት ይገባል። ተግባራዊ እየተደረገ ያለው
ፖሊሲ ግን በዚህ መልኩ የወጣ አይደለም። ፖሊሲው ከወጣ በኋላም ለማስፈጸም የነበረው የማነጅመንት ስርዓት አገራችን
ውስጥ ካለው የጸጥታ፣ የደህንነትና የውጭ ጉዳይ ሁኔታ ጋር የሚመጣጠን አልነበረም።
አዲስ ዘመን፡- ፖሊሲው ከአወጣጡ እስከ አፈፃፀም እርስዎ አልተሟሉም የሚሏቸው ነገሮች ባለመካተታቸው በአገር ላይ የደረሰ ጉዳት ብለው በማሳያነት ሊያቀርቡልኝ የሚችሉት ጉዳይ ይኖራል?
ሌተናል ጀኔራል ገብረፃድቃን፡- ለእኔ
ግልጽ የሆነውና ቀድሞ የሚመጣው አምና በአገራችን ላይ ተከስቶ የነበረው ብጥብጥና ሁከት ነው። ችግሮችን አስቀድሞ
የሚተነተንበት ስርዓትና አሰራር ቢኖር ኖሮ አስቀድሞ ሊታይ ይችል ነበር። ይህ ባለመሆኑ የሰው ህይወት ሊጠፋ፤
ንብረት ሊወድምና የአገሪቱ ዕድገትም ወደ ኋላ ሊጎተት ችሏል። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ነው ችግሩ ጋብ ያለው። ከዚህም
በላይ አሁን ያልተከሰተ ወደፊት ሊከሰት የሚችል እያረገዘ ያለ ነገር ሊኖር ይችላል። እንዲህ ዓይነት አሰራርና
ዝግጅት ባለመኖሩም ጭምር ነው የኤርትራ ጦርነት በድንገት ወደ እኛ የመጣብን። ከጦርነቱ በኋላ በመሠረታዊነት
ከገመገምናቸው ነገሮች አንዱ የብሔራዊ ደህንነትና ጸጥታችን በአጠቃለይ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያችን ጉዳዩ በሚጠይቀው ልክ
የአሠራርና ዝግጁነት አለመኖሩን ነው። ከዚህ ቀደም ከገጠሙን አደጋዎች በላይ ሊያጋጥመን የሚችልበት ሁኔታ ዝግ
አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ በጎረቤት አገራት ላይ እየተገበረች ያለችው የውጭና የደህንነት ፖሊሲ ውጤታማ ነው ብለው ያምናሉ?
ሌተናል ጀኔራል ገብረፃድቃን፡-ጎረቤቶ ቻችን በርካቶች ናቸው። ከኢትዮ- ኤርትራ
ጦርነት በኋላ የኢትዮጵያ ተቀባይነት በጎረቤቶቻችን እያደገ መጥቷል። በመሰረቱ ፖሊሲው በአገር ውስጥ ላለው ሥራ
ደጋፊ እንዲሆን ተደርጎ ተቀርጿል። ከመንግሥት መዋቅር የወጣ መረጃ ባይኖረኝም በውጭ እንደማየው ለውጥ አምጥቷል
የሚል እምነት አለኝ። ከኤርትራ ጋር ያለው ግንኙነት ከጦርነቱ በኋላ ሰላምም ጦርነትም ያልሆነበት ችግር ነው።
ከሱዳን ጋር ጥሩ ግንኙነት አለ የሚባል ነገር እሰማለሁ። ግንኙነቱ ምን ያህል ጠንካራና ስልታዊ ነው የሚል ጥያቄ
አለኝ። ደቡብ ሱዳን እንደ አገር ለመቆም የኢትዮጵያ አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነበር። አሁን በደቡብ ሱዳን ላይ ጥሩ ፖሊሲ
ነው ያለው ብዬ አልወስድም። ምክንያቱም ትልቅ ትርምስ ውስጥ ነው ያለችው። ደቡብ ሱዳን ወስጥ ያለውን የፖለቲካ
ቅርጽ የሚያስይዙት ከኢትዮጵያ ይልቅ ኡጋንዳ፣ ሱዳን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ግብጽ እየሆኑ ነው።
ጅቡቲ
ለኢትዮጵያ ትልቅ ስልታዊ አገር ናት። የንግድ እንቅስቃሴያችን የሚመሰረተው በዚህ ላይ ነው። በኢኮኖሚው እንቅስቃሴ
መልካም ግንነኙነት እንዳለ እሰማለሁ። ነገር ግን በጅቡቲ ከጅቡቲ ውጭ ያሉ ሀይሎች በርካቶች ናችው። አሜሪካኖች፣
ፈረንሳዮች፣ ቻይናና ሌሎች አገሮች እየገቡ ነው። የዓለም አቀፍ ሀይሎች መሰባሰቢያና የእነሱ ፖለቲካ የሚተገበርበት
አገር እየሆነ ነው። እንደዚያ ሆኖ የእኛ ደህንነት አስተማማኝ ሆኖ ይቀጥላል አይቀጥልም ትልቅ ጥያቄ የሚያስነሳ
ነገር ነው። ጥብቅ ክትትልና የሚያስፈልገው ጉዳይ ነው።
ከሁሉ
በላይ ግን ኢትዮጵያ ትልቅ አገር እንደመሆኗ በቀይ ባህር አካባቢ የሚደረግ ነገር ሁሉ ያሳስበናል። እኛ ከቀይ
ባህር የተነጠልን አገር ልንሆን መፍቀድ የለብንም። ቀይ ባህር አካባቢ በኤርትራ መንግሥት ሳቢነት፤ በእራሳቸው
ፍላጎትም የሳውዲ ዓረቢያ፣ ዩናይትድ ዓረብ ኤምሪትና ግብጽ የጦር ሰፈር አቋቁመዋል ይባላል። ይሄንን ጉዳይ የእኛ
የውጭ ጉዳይና አገራዊ ደህንነት ፖሊሲያችን እንዴት ነው የሚያየው። የሚከተለው አካሄድ ውጤታማ ነወይ? ከተባለ ውጤታማ ነው ብዬ አላስብም። እንደገና መታየት አለበት የሚል ትልቅ አመለካከት አለኝ።
ከኬንያ
እና ኡጋንዳ ጋር ብዙም ችግር የለብንም። የግብጽ ጉዳይ ከዓባይ ጉዳይ ጋር ብቻ መታየት የለበትም። የዓባይ ጉዳይ
ለእኛም ለእነሱም ያሳስባል። ግን አጠቃላይ እንቅስቃሴያቸው ከዚያ የበለጠ ነው። በምስራቅ አፍሪካና በተቀረው አፍሪካ
ብሎም በገልፍ አገሮች ትልቅ ተፅዕኖ እንዲኖራቸው ይፈልጋሉ። ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ዝምድና ከዚህ ጋር አያይዘው
ነው የሚያዩት። እኛ ይህን ጉዳይና እንቅስቃሴ በሚገባው ስፋትና ጥልቀት እያየነው ነወይ? የሚሉት ጉዳዮች መነሳት አለባቸው።
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያና ኤርትራን ሁኔታ መቀየር ይቻላል ብለው ያምናሉ?
ሌተናል ጀነራል ገብረፃድቃን፡- አሁን
ያለውን የኢትዮጵያና የኤርትራ ሁኔታ መቀየር ይቻላል ብዬ አምናለሁ። ምክንያቱም ኢትዮጵያና ኤርትራ አንድ አገርና
ህዝብ ሆኖው የቆዩ ናቸው። ከዚያ በኋላ ደግሞ የሆነው ይታወቃል። አሁን ባለው ሁኔታ የሁለቱ አገር ህዝቦች
ወዳጅነትና አንድነት ለጊዜው ተሸፍኗል እንጂ አልጠፋም የሚል እምነት አለኝ። በሌላ በኩል ግን አሁን ስልጣን ይዞ
ያለው የኢሳያስ አፈወርቂ መንግሥት ይህ እንዲጠፋ ብቻ ሳይሆን ለወደፊትም ቢሆን በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ እንዲፈጠር
የቻለውን ሁሉ እያደረገ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የሁለቱ አገራት ግንኙነት ሲመለስ ወደ ምን ያመራል ብለው ያስባሉ?
ሌተናል ጀኔራል ገብረፃድቃን፡- ይህ
አስቸጋሪ ነው። ሁለቱ ህዝቦች የሚወስኑት ነው። በመጀመሪያ በነፃ የሚገናኙበትና ሀሳባችውን የሚቀያየሩበት
በመሀከላቸው ያለውን ልዩነት የሚያስወግዱበት ሁኔታ መፍጠር ነው ትልቁ ጉዳይ። ከዚያ በኋላ የሁለቱ ህዝቦች ውሳኔ
ይሆናል። ያለፈውን ግንኙነትና አሁን በኤርትራ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለው በደል፣ ጭቆናና ግፍ የዚያች አገር
መንግሥት ከተነሳ በኋላ ሁኔታው በእራሱ መደበኛ ሁኔታ ይመለሳል ብዬ አስባለሁ። ምናልባት አሁን ባለው ሁኔታ አንድ
አገርና ህዝብ ይሆናሉ ማለት ይከብዳል። በቀጣይ ግን በቅርብ ጊዜ በጣም እርስ በእርሳቸው የሚተሳሰቡ ለሁለቱም
አገሮች ጥቅም የሚያስቡና አስተዋፅኦ የሚያደርጉ የቅርብ ወዳጆች ሊሆኑ ይችላሉ።
አዲስ ዘመን፡-መንግሥት በኤርትራ ላይ ሲከተል የነበረው የተመጣጣኝ እርምጃ ፖሊሲ ምን ያህል ውጤት አምጥቷል ብለው ያስባሉ?
ሌተናል ጀነራል ገብረፃድቃን፡- ምናልባት
ለመጀመሪያው አስር ዓመት ውጤት አምጥቶም ከሆነ ከሶስት ዓመት ወዲህ ግን ውጤት እያመጣ እንዳልሆነ እየታየ ነው።
የኢሳይያስ መንግሥት ከምስራቅና ከገልፍ አገራት ጋር በቀይ ባህር ለማስፈር እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ በአንድ በኩሉ
የኤርትራን የኢኮኖሚ ቸግር እየፈታላቸው ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ጡንቻቸውን እያሳደጉ እየመሰላቸው ዋስትና
እየሰጣቸው ነው። በዘላቂነት ደግሞ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ለመንቀል የሚያስቸግር አስቸጋሪ ችግር እየፈጠሩ
ነው ያሉት። ስለዚህ ፖሊሲው መጀመሪያ ላይ ሲወጣ እንዲህ ዓይነት ችግር ይፈጠራል ብሎ ያሰበ ስለመኖሩ እጠራጠራለሁ።
በመሆኑም ፖሊሲው አሁን ካለው ሁኔታ በመነሳት ምን ማድረግ አለብን ማለት ያለበት ይመስለኛል።
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ መንግሥት በአሸባሪነት የፈረጃቸው የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች ግብጽና ኤርትራን በመ ጠቀም የሚያደርሱት ጉዳትን እንዴት ያዩታል? ምንስ እርምጃ መወሰድ አለበት ይላሉ?
ሌተናል ጀነራል ገብረፃድቃን፡- መንግሥት
በአሻበሪነት የፈረጃቸው በአንድ በኩል በትጥቅ ትግል ስልጣን ለመያዝ በሌላ በኩል ህዝቡን በፕሮፓጋንዳ ለመከፋፈል
የሚፈልጉ ሀይሎች የኤርትራንና የግብጽን ሀይል ተጠቅመው ኢትዮጵያ ውስጥ ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ያመጣሉ ብሎ
መመኘት የዋህነት ነው። በዚህ አይነት መንገድ የሚመጣ ለውጥ የለም። የሚመጣ ለውጥ ካለም አገር ውስጥ ያለው ህዝብ
እሱ ይጠቅመኛል ብሎ በሚያስበው የአስተሳሰብ ስልት ተደራጅቶ በሚያደርገው ትግል ነው የሚመጣው። እነሱ የሻዕቢያ
ተላላኪ ለመሆን ካልሆነ በስተቀር አሁን በሚሄዱበት መንገድ አገር ውስጥ ዘላቂ የሆነ ሰላም፣ ልማት፣ዴሞክራሲ ያመጣሉ
ብሎ ማሰብ አይቻልም። ከዚህ አንፃር መንግሥት እነሱን ለመቆጣጠር የሚያደርገውን ጥረት ማጠናከር አለበት።
የሁሉም
ችግር መነሻ ብዬ የማስበው አገር ውስጥ ያለው የፖለቲካ ችግር ነው። በሁለተኛ ደረጃ ይህን ለመጠቀም የተዘጋጁ
እንደ ሻዕቢያ የመሰሉ ሀይሎች መኖራቸው ነው። አገር ውስጥ ያለው የፖለቲካ ችግር ለእነሱ ተብሎ ሳይሆን ለአገር
ሰላም፣ ልማትና ብልጽግና ተብሎ መፈታት አለበት።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ በኤርትራ ላይ ምን አይነት አካሄድ መከተል አለበት ብለው ያስባሉ?
ሌተናል ጀነራል ገብረፃድቃን፡- የኢትዮ
ጵያ መንግሥት ከኤርትራ ጋር ያለውን ግንኙነት በሚከልስበት ወቅት በእኔ አስተሳሰብ ሁለት መሰረታዊ ነገሮችን ይዞ
መነሳት አለበት። አንደኛው የኤርትራና የኢትዮጵያ ህዝብ ወዳጅነትን ይበልጥ በማቀራረብ የኤርትራ ህዝብ የኢሳይያስ
መንግሥት ከአሰባሰባቸው ቡድኖች ነጥሎ በማውጣት ህዝቡ የእራሱን የወደፊት ጥቅም የሚያይበትን መንገድ እንዲከተል
ማድረግ ይገባል። ለዚህም የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ደጋፊ መሆኑን በፖሊሲም በተግባርም የሚያረጋግጥ ነገር ማድረግ
ተገቢ ይመስለኛል። በመሰረቱ የኤርትራ መንግሥት ጉዳይ የኤርትራውያን የእራሳቸው ጉዳይ ነው። ግን ካለን ታሪካዊ
ግንኙነትና ቅርበት አንፃር ትልቅ ሚና መጫወት እንችላለን። ይህ ሚናችንን የሁለቱም ህዝቦች ግንኙነት በሚያጠናከርና
የኤርትራውያን ሰቆቃ በአጭር ጊዜ የሚጠናቀቅበትን መንገድ በማሰብ መፈጸም አስፈላጊ ነው።
ሁለተኛው
አሁን ኤርትራ ላይ ያለው መንግሥት እድሜው የሚያጥርበትን መንገድ ማስቀመጥ የሚያስፈልግ ይመስለኛል። እድሜው
የሚያጥርበት ብዙ መንገዶች ሊኖሩ ይችላሉ። ዋነኛው ከኤርትራ ህዝብ እየተነጠለ እየተዳከመ አገሪቱን
በማያስተዳደርበትና አካባቢውን በማያተራምስበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ ማድረግ ያስፈልጋል። ጊዜ ባገኘ ቁጥር ስር
እየሰደደ ስለሚሄድና የህዝቦቿን ሰቆቃ የሚጨምር ነው። ስለሆነም የኢኮኖሚና ፖለቲካ ዲፕሎማሲ በመጠቀም አስፈላጊ ሆኖ
ከተገኘም ከኤርትራውያን ጋር በመሆን ወታደራዊ አቅምን በመጠቀም ጭምር እድሜው የሚያጥርበትን መንገድ መፈለግ
አስፈላጊ ነው። ይህ ቀላል እንደማይሆን አውቃለሁ። ግልጽና የረጅም ጊዜ ፖሊሲ አስቀምጦ እየተሰራ ከሄደ ግን እየጠራ
ይሄዳል።
አዲስ ዘመን፡-በእርሰዎ እምነት የኢይሳያስ መንግስት አሁን እየሄደበት ያለውን አካሄድ የመቀየር እንጥፍጣፊ ተስፋ የለውም?
ሌተናል ጀኔራል ገብረፃድቃን፡- አሁን
ኤርትራ ላይ ስልጣን ይዞ ያለው ቡድን ስልጣን ላይ እስካለ ድረስ ከኢትዮጵያ ጋር ጥሩ ግንኙነት ይኖራል ብሎ ማሰብ
አይቻልም። ምክንያቱም ብዙ ነገሮችን ያደረገለትን መንግሥት ነው ዞሮ በሳንጃ ጀርባውን የወጋው። ስለሆነም
ከጦርነቱም በፊት ሆነ በኋላ ለኤርትራ መንግስት የሚመች መንግሥት ይኖራል ብዬ አላስብም።
አዲስ ዘመን፡- አሁን 62 ዓመትዎ ነው። እስካሁን ባለዎት የሥራ ውጣ ውረድና አብርክቶ የሚቆጭዎት ነገር አለ?
ሌተናል ጀነራል ገብረፃድቃን፡- ምንም
የለም። እኔ እድለኛ ነኝ። እድለኛ ማለት ከትምሀርት ቤት ወደ ትግል ሄድሁኝ። ተዋጋሁኝ። ከእኔ ጋር በትግሉ ሜዳ
የነበሩ ብዙ ጀግኖች ጓደኞቼና ወንድሞቼ በረሃ ላይ ቀርተዋል። እኔ በህይወት ተርፌያለሁ። በኋላም የመንግሥት
ሀላፊነት ተሰጠኝ። በተለይ አገራችን በኤርትራ በተጠቃችበት ወቅት አቅሜና ችሎታዬ የፈቀደውን ሁሉ በማድረግ የአገሬን
ክብር ለማስመለስ ጥረት አድርጌያለሁ። ከዚያ በላይ ውጤቱ ሊሄድ ይችል ነበር ወይ? ይህ
ሁል ጊዜም በክርክር ውስጥ እንደሆነ አውቃለሁ። ከወጣሁ በኋላ እንደማንኛውም ኢትዮጵያ ሰርቼ ልጆቼን አሳድጊያለሁ።
አሁን አያት ሆኛለሁ። በጣም ደስተኛ ነኝ። የሚቆጨኝ ነገር የለም። በዚህ መንገድ ማለፌም እድለኛ ነኝ ብየ ነው
የማስበው።
አዲስ ዘመን፡- ወደ ኋላ ተመልሰው አስተካክሉት ቢባሉ የሚያስተካክሉት ነገር ይኖር ይሆን?
ሌተናል ጀነራል ገብረፃድቃን፡- እንደ ድርጅት የሚታይ ነገር ሊኖር ይችላል። እንደ ግሌ ግን ሁሉንም ወደ ኋላ ተመልሼ ያደረኩትን ነገር ሳስብ ሁሉን ያደረኳቸውን ነገሮች እንደገና እደግማቸው ነበር። ለእኔ ፈታኙ የነበረው በ1993 ዓ.ም የህወሓት መከፋፈል ነበር። አሁን ተመልሼ ሳስብ ያንጊዜ ያደርኩትና የተናገርኩትን ዛሬም አድርገው ነበር። እንደ ግለስብ ግን ይህን ባድርግ የምለው ነገር የለም።
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡኝ ጊዜና ማብራሪያ በጣም አመሰግናለሁ።
ሌተናል ጀኔራል ገብረፃድቃን፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ተኽለሃይማኖት ገብረመድህን
No comments:
Post a Comment