Wednesday 14 June 2017

የህወሓት(ትግራይ ህዝብ) የትግል ጉዞና የቀጣይ ዘመን ተልዕኮ(ለፍትህና እኩልነት የተከፈለ ዋጋ)

የህወሓት(ትግራይ ህዝብ) የትግል ጉዞና የቀጣይ ዘመን ተልዕኮ(ለፍትህና እኩልነት የተከፈለ ዋጋ)

ለፍትህና እኩልነት የተከፈለ ዋጋ
የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በወቅቱ በነበረ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት  ህወሓት(ትግራይ ህዝብ)    ወጣቱ ሲያነሳቸው ከነበሩት ጥያቄዎች የህዝባዊ መንግስት ምስረታ፣ የእኩል ተጠቃሚነት፣ የብሄርና የኃይማኖት እኩልነት፣ የፍትህና ዴሞክራሲ ጥያቄዎችን ለመመለስ በኢህአዴግ ጥላ ስር ሆነው በፅናት የትጥቅ ትግል አካሂደዋል። በርካታ መስዋዕትነትም ከፍለዋል። ብረት አንስተው በትጥቅ ትግሉ ፍልሚያ የተሳተፉ ታጋዮች ብቻም ሳይሆኑ ንፁሃን የአገራችን ጭቁን ህዝቦች በደርግ የጦር አውሮፕላኖች ዘግናኝ በሆነ መልኩ በጋራ የተፈጁባቸው እንደ ሀውዜን፣የጭላ፣መርሳና በለሳ ያሉ መንደሮች ለፍትህ፣ ለዴሞክራሲና ለብሄር እኩልነት መረጋገጥ ሲባል የተከፈሉ መራር መስዋዕትነቶችን አጉልተው አሳይተዋል። በደርግ የአፈና መዋቅር ከመማረክ ራስን ማጥፋትን የመረጡ ወጣት ታጋዮች ህወሓት በደርጎች እጅ ወድቀው እንኳ ከቆሙለት ዓላማ ፍንክች እንዳላሉ አረጋግጠዋል።  ጓዶች አሞራው (ወልደገሪማ)፣ ቐሺ ገብሩ (ሙሉ ገብረእግዚያብሄር) ፣ማርታ (ካሕሳ)  ያሉ በደርግ የግፍ በትር የተገደሉ ታጋይ የኢትዮጵያ ወጣቶች የኢህአዴግ የዓላማ ፅናትና ለህዝቦች ጥቅም ሲባል የተከፈለ መስዋዕትነት የሁልጊዜም ማነፃፀሪያዎች ናቸው። ደርግ ሲያደርሰው ከነበረው ጭፍጨፋ ባሻገር የአገሪቱን ኢኮኖሚ በማዳከም ህዝቡን ለከፋ ድህነት ዳርጓል።

በገጠሩ የአርሶ አደሩን ምርት ከመንጠቅ ባሻገር ገበሬው ከምርት ተግባሩ ተፈናቅሎ በማያምንበት ጦርነት በግዳጅ ለወታደርነት እንዲሰለፍም አድርጓል። የገጠርና የከተማ ወጣቶችን ከያለበት በማፈስ፣ የተቃወሙትንም እስከ መረሸን በደረሰ እርምጃ በመግደል ወጣቶችን በጦርነት ማግዷል። በተለይ አርሶ አደሩ በስርዓቱ ባለሟሎች ዶክተር ሓጎስ ግደይ አንዱ ናቸው። በብሄራዊ ውትድርና ሰበብ በግዳጅ ሲታፈስ የነበረው ወጣት ይደርስበት የነበረው መከራ የማይረሳ ነው ይላሉ። ዶክተር ሓጎስ  “በዘመኔ አደን እንደሚወጣ ሰው ተማሪ እየተጠበቀ በደርግ የደህንነት ሀይሎችና በቀበሌ አብዮት ጥበቃ ጓዶች ይታሰርና ይረሸን ነበር እንጂ ወጣቱን ለስራ ፈጠራ የሚያበረታታ ሁኔታ ፈፅሞ አልነበረም” በማለትም ያስታውሳሉ። በዚህም ምክንያት ወጣቱ መጓዝ ወደነበረበት ትክክለኛ አቅጣጫ መጓዝ ባለመቻሉ ያልተፈለገ መስመር ተከትሏል፤ ለቅብብሎሽ የሚመች የለውጥ እርሾ አጥቶ ህይወቱን ወዳልተፈለገ መስመር መርቷል በማለት ይገልፃሉ። “እኔ በዚያ አደጋ ውስጥ የሾለክሁ፣ አሁን ያለው ስርዓት በመምጣቱም እንደገና ወጣት የሆንኩ፣ በዚህ ዘመን ትኩስነት የሚሰማኝ የዚህ ዘመን ወጣት ነኝ” በማለት ራሳቸውን ከዘመኑ ወጣት አዲስ ተስፋና አዲስ እድል ጋር አያይዘው ይመለከታሉ። የደርግ ሊቀመንበር መንግስቱ ኃይለማርያም ዩኒቨርስቲ ድረስ መጥቶ ተማሪዎችን ትዘምታላችሁ ወይስ አትዘምቱም? ብሎ ሲጠይቅ እዚያው ዩኒቨርስቲ ግቢ ውስጥ ነበርኩ የሚሉት ዶክተር ሓጎስ ፣ የወቅቱ ገጠመኛቸውን እንዲህ ያብራራሉ። የደርግ ሊቀመንበር መንግስቱ ኃይለማርያም “ልደት አዳራሽ” ተገኝቶ ተማሪዎች እንዲዘምቱ ጥሪ አቀረበ። እሱ በመጣበት ወቅት ሁለተኛ ዲግሪዬን እየሰራሁ ስለነበር ከቤተመፃህፍት አልወጣም ነበር። በዚያ ሰሞን ግቢ ውስጥ ፈፅሞ የማታስባቸውን ነገሮች ታያለህ፤ የምታስበውን እንኳ መግለፅ የማትችልበት ሁኔታ ነበር። የፖለቲካ ካባ የለበሱ የተለያዩ ሰዎችን ታያለህ። ተማሪው ወጣትና አዲስ ሀይል በመሆኑ ማን እንደሚመራው ሳያውቅ በውስጡ ያሉ የደርግ ሰዎች በቀየጎንደርዱለት መንገድ ተታሎ አብሮ እንዘምታለን ይላል። ወዴት እንደሚዘምት ግን አያውቅም። “በእንዘምታለን መፈክር ውስጥ ወደ ዘመቻ የሚቀሰቅሱ፣ የተማሪ ልብስ ለብሰው ግፊት የሚያደርጉ ሌሎች ሀይሎች ነበሩ። በወቅቱ ከምላስ ላይ ቃላት ቀልቦ ትርጉም መስጠት ቀላል ነበር። ሊቀመንበር መንግስቱ ያደረገው ይሄንኑ ነው። ከመንግስቱ ኃይለማርያም ጀምሮ ያሉ የደርግ አመራሮች በወጣት ተማሪዎች ላይ ጫና በመፍጠር አደገኛ ውሳኔ ወስነዋል። አምባገነኑ የደርግ ሊቀመንበር ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም በውድቀት አፋፍ ላይ በነበረበት ወቅት ወጣቱን በብሄራዊ ውትድርና ግዳጅ  ከየቤቱ ያሳፈሰና የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታቸው አስነስቶ በግዳጅ እንዲዘምቱ ያደረገ ቢሆንም በወጣቶች የተደራጀው ህወሓት(ትግራይ ህዝብ) መላውን ህዝብ በማሰለፍ፣ በትጥቅ ትግሉም ድል በመጎናፀፍ እያየለና እየበረታ መጣ። ይህም በደርግ ላይ ተስፋ መቁረጥ አስከተለ። በዚህ ወቅት በአደባባይ በጠርሙስ የተሞላ ደም በመድፋትና ቀይ ሽብርን በማፋፋም ቀዳሚ ሚና የነበረው፣ ወጣቱን አማራጭ በማሳጣት ለሞትና ስደት ሲዳርግ የቆየው፣ መረሸን የገበጣ ጨዋታ ያህል የሚቀለው የስርዓቱ መሪ መንግስቱ ኃይለማርያም፣ ግራ በመጋባት ለራሱና ለባለስልጣኖቹ አዲስ የፍልስፍና ጥያቄ ይዞ ቀረበ። “…እውን እኛ ህዝቡን እናውቀዋለን? ህዝቡስ በእውኑ እኛን ያውቀናል? የሚል ጥያቄ አሳድሮብናል። እውን ህዝቡስ የሚፈልገውን ያውቃል ወይ? የሚለውም ጥያቄ አድሮብናል። ራሱንስ በትክክል ይገልፃል ወይ? የሚሉት ጥያቄዎች በአጠቃላይ እንቅልፍ ነስተውናል።…” የደርጉ መሪ ስርዓቱ ከህዝቡ መነጠሉን ተስፋ በቆረጠ አንደበት እየገለፀና ህዝቡ የሚፈልገውን አያውቅም ብሎ እየተሳለቀ በነበረበት በዚህ ወቅት በትጥቅ ትግል ላይ የነበረው ህወሓት(ትግራይ ህዝብ) የደርግን ግብዓተ መሬት ለመፈፀምና የኢትዮጵያ ህዝቦች ለዘመናት ሲናፍቁትና ሲታገሉለት የነበረውን ጥያቄ በተግባር ለመመለስ እየተዘጋጀ ነበር። ከዚሁ ጎን ለጎን በህዝቡ ላይ አንዳች ችግር ሳይከሰትና ሁሉም ተቃዋሚ ወገኖች በሚሳተፉበት የሰላምና የሽግግር ጉባኤ ለማዘጋጀት እያቀደ ነበር።   የኢህአዴግ ምክር ቤት አባልና የወቅቱ ከፍተኛ የትግል መሪ ጓድ አባይ ፀሃዬ ይህንኑ በማስመልከት ከሚነግረን የምንረዳው ህወሓት(ትግራይ ህዝብ) የሃይል የበላይነት እያለው እንኳ ደም አፋሳሹ ጦርነት ቆሞ ሰላማዊ ሽግግር እንዲደረግ በእጅጉ መስራቱን ነው። እነሆ... “በ1981 ዓ.ም የሰላም ጉባኤ መደረግ አለበት የሚል ሃሳብ መጣ። ጉባኤው ሁለት ጥቅም ነበረው። አንደኛው ደም መፋሰስ እንዳይኖር ያደርጋል፤ የሀይል የበላይነት እያለንም ቢሆን ለሰላም መቆማችንንም ያሳይልናል። በእብሪትና ማን አለብኝነት አንሄድም ብለን አቋም በመውሰድ ተጨማሪ ደም መፍሰስ የለበትም፤ ህይወትና ንብረት መጥፋት አይኖርበትም ብለን ወስነናል። ይህን ሀሳብ ህዝቡና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ይቀበለዋል የሚል እምነት ነበረን። ደርግ መደምሰሱ ባይቀርም የሰላም ሀሳቡን ከተቀበለው ይሳተፍ ብለን ነበር። ... ብዙዎች የዓለማችን አገሮች ከጦርነት በኋላ ስልጣን ጠቅልለው በሚይዙበት ሁኔታ ህወሓት ስልጣን የህዝብ መሆኑን በማወጅ በዴሞክራሲያዊ አግባብ የህዝብ ስልጣንና ወሳኝነትን አምኖ ለሰላም ቆሟል። በዚህ ጤናማ አሰተሳሰቡ ወጣቱን ከጥፋት ታድጓል፤ አገራችንንም ከብተና አድኗል።” ህወሓት ደርግን ለመደምሰስ በተቃረበበት በዚሁ ጊዜም ቢሆን የትኛውም ሀይል ከህዝቡ ፍላጎትና ውሳኔ ሊወጣ አይገባም የሚል ፅኑ አቋም ነበረው። በዚህም ምክንያት ሁሉም ተቃዋሚ ሀይሎች በሰላማዊ ሽግግሩ እንዲሳተፉ፣ ህዝቡም እንዲያውቃቸው መደረግ አለበት የሚል የሁልጊዜም እምነቱን በተግባር እንዳሳየ ጓድ አባይ ያስታውሳል። ደርግ ሲደመሰስ ግርግርና ህይወት መጥፋት እንዳይከሰት፣ ትርምስና ስርዓት አልበኝነት እንዳይኖር ምን እናድርግ ብሎ ህወሓት መወያየጎንደርቱንና የሽግግር መንግስቱ በህዝብ መመስረት እንዳለበት መወሰኑንም ያስታውሰናል። ጓድ አባይ እንደሚገልፀው ህወሓት በሀገር ውስጥም በውጭም ያሉ የፖለቲካ ሀይሎች ተሰባስበው የሽግግር መንግስት እንዲያቋቁሙ፣ ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲታወጁ በማድረግ እንዲሁም ሁሉም ወገን አማራጩን በማቅረብ ህዝቡ የሚሳተፍበት ህገመንግስት እንዲያረቅቁ ቀድሞውኑ ተዘጋጅቷል። በዴሞክራሲያዊ ምርጫ መንግስት እንመሰርታለን ብሎም አቋም ይዟል። ይህን በሀይል የሚቃወም ቢኖር ተገድዶ ወደ ጦርነት ሊገባ እንደሚችልም አስቀድሞ ተንብዮአል። ህወሓት በ1983 ሰው በላውን የደርግ ስርዓት በህዝብ ትግል በመገርሰስ አገሪቱን ሲቆጣጠርም ቀዳሚው የወጣቱ ጥያቄ የዴሞክራሲ ጥያቄ መሆኑን ተረድቶ በራሱ በወጣቱ ትግል በተመሰረተው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ምላሽ ሰጥቷል። በሽግግር ቻርተሩ የሃይማኖት እኩልነት፣ የእምነት ነፃነት፣ የብሄርና የጾታ እኩልነት፣ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት ያለገደብ እንዲከበሩ አድርጓል። የትግራይ ህዝብ ለረጅም ዓመታት እልህ አስጨራሽ ትግል በማድረግ ባስመዘገቡት ስኬት የአገራችን ህዝቦች ለረጅም ዓመታት የታገሉለት የህዝቦች የዴሞክራሲ መብት ዳግም ለጭቆና እንዳይጋለጥም አድርጓል። በተለይም ወጣቶች የተሰዉለት የመደራጀትና ሃሳብን በነፃ የመግለፅ መብት ዋስትና እንዲኖረው አስችሏል። የደርግ ስርዓት በተወገደ በአንድ ወር የስልጣን ቆይታውም በደርግ ታስረው የነበሩ የፖለቲካ እስረኞችን በሙሉ በነፃ ለቅቋል። ለአስራ ሰባት ዓመት ፀንተው የቆዩ የሰዓት እላፊ አዋጆችን አንስቷል። ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስና ሃሳብን በነፃ የመግለጽ መብት ያለገደብ እንዲከበር በማድረግ የወጣቱን ነፃነት አረጋግጧል፤ ለወጣቱ ያለውን ወገንተኝነትና ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ያለውን ቁርጠኝነትም በተግባር አሳይቷል። ይህ በህወሓት ፅናትና ህዝባዊ ትግል የመጣ ውጤት ነው። ፍትህና ዴሞክራሲ በሌለበት ያለ ፍርድ በየአደባባዩ የተገደሉ፣ ስቃይና መከራን የተቀበሉ በርካታ የህዝብ ልጆች በህወሓት መሪነት በደማቸው ጭቆናውን አሸንፈውና እልፍ ሆነው አዲስ የህዝቦች ስርዓት መስርተዋል። ህወሓት ደርግን አስወግዶ አገሪቱን ሲቆጣጠር አንድ የዓድዋ አዛውንት በቀይ ሽብር የሞተ ልጃቸውን ፎቶ ግራፍ ይዘው በመቅረብ ከዚህ በታች የሰፈረውን ታሪክ አጫወቱኝ ብሎ ህወሓትን ከመሰረቱ ጓዶች አንዱ ታጋይ ኣቦይ ስብሓት ነጋ የገለጸልን በዓድዋ ብቻ ሳይሆን በሌሎቹ የኢትዮጵያ ከተሞችና ገጠሮች የነበሩ ወጣቶች በፍትህ እጦት ያሳለፉትን ግፍና መከራ ያስታውሰናል።… “ልጄ በደርጎች ዛሬ ታሰረ፤ በነጋታው ተገደለ። ነገር ግን በሶስተኛው ቀን ወንጀል የለበትም ተብሎ ከሚፈቱ ሰዎች ጋር ከእስር ቤት ስሙ ተጠራ። ልጄ እንደ ሌሎቹ ወጣቶች ፀረ መንግስት ሆኗል ተብሎ ወንጀለኝነቱ ተረጋግጦ ቢገደል ኖሮ ባልቆጨኝ። ያለ ጥፋቱ ተገደለ፣ ከሞተ በኋላ ነፃ ነው ተባለ። ይሄ መቼም ከሆዴ ሊወጣ አይችልም”። ያለ ፍርድ የተፈፀሙ ዘግናኝ ግድያዎች እጅግ ብዙ አስረጂ አላቸው። ማን ምን ፈፀመ የሚለው ሳይጣራ በየአደባባዩ የተገደለው ወጣት ለቁጥር ይታክታል። ያለፍርድ ግድያ ከተፈፀመባቸው በኋላ ነፃ ናቸው ተብለው ከእስር ቤት ስማቸው የተጠራ ወጣቶችን በርካታ ከተሞችና በርካታ ቤቶች ያውቋቸዋል። ፍትህን የጠየቀ፣ ህዝባዊ መንግስት ይመሰረት ብሎ የተሰለፈ፣ የኃይማኖትና የብሄር እኩልነትን ያቀነቀነ ወጣት እጣው ሞት ነበር። ያለ ፍርድ ከተገደሉት የትላንቶቹ ወጣቶች የአደራ ቃል የተረከቡት የዛሬዎቹ ወጣቶች የትግሉ አቅጣጫ በቅብብሎሽ ከፀረ ደርግ ወደ ፀረ ድህነት ትግል እንዲዞር አድርገዋል። ያለ ፍርድ ለገደሏቸውም በፍትህ አደባባይ ምህረት ሰጥተዋል። በጭቆናው ዘመን በወጣትነት ትኩሳታቸው ላይ ያረፈውን የማይረሳ አሻራ “መቼም እንዳይደገም” ብለው የኢትዮጵያን ዴሞክራሲ በትውልድ ቅብብሎሽና የመተካካት መርህ የከፍታ ማማ ላይ አኑረዋል። የዓለማችን አይኖች ኢትዮጵያ ላይ አርፈው፣ የኢትዮጵያንም አካባቢያዊ ድጋፍ ሽተው የተገኙት እኒያ የዚያ ዘመን ወጣቶች በማያረጅ አስተሳሰብ ዛሬም የአገሪቱ ባለአደራ ወጣቱ ነው ብለው ለኢኮኖሚ እኩል ተጠቃሚነት፣ ለኃይማኖት እኩልነት፣ ለፍትህና ዴሞክራሲ እውንነት፣ ለብሄርና ማንነት ጥያቄዎች መከበር ዘላቂ ምላሽ መስጠታቸውን ቀጥለዋል። 

በጋዜጠኛ ተኽለሃይማኖት ገብረመድህን ከባህር ዳር

No comments:

Post a Comment

TEKLEHAIMANOT JOCO

በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ የተነሳ የእሳት ቃጠሎ በንብረት ላይ ጉዳት አደረሰ

ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ ከኤሌክትሪክ ኃይል ጋር ተያይዞ ዛሬ በተነሳ የእሳት ቃጠሎ በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ዩኒቨርስቲው አስታወቀ። በቃጠሎው በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት እንደሌለም ተመልክቷል። የዩኒቨርስቲው ...