Saturday 3 June 2017

በመቀሌ የተከፈተው የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ኤክስፖ የንግድ ትስስር እንዲኖር ምቹ ሁኔታ መፍጠሩ ተገለጸ

በመቀሌ የተከፈተው የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ኤክስፖ የንግድ ትስስር እንዲኖር ምቹ ሁኔታ መፍጠሩ ተገለጸ

የተከፈተው የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ኤክስፖ ምርታቸውን ወደ ገበያ በማቅረብ የንግድ ትስስር እንዲኖር ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው የኤክስፖው ተሳታፊ የማምረቻ ተቋማት ተጠሪዎች ገለጹ፡፡
ተሳታፊዎቹ እንዳሉት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ መነቃቃት እያሳየ ነው፡፡
የዘርፉ መነቃቃት ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኙ ከፍትኛ ኢንዱስትሪዎች በኤሌክትሪክ ሀይል የሚሰራ የውሃ ማሞቂያ ምርት እያቀረቡ መሆናቸውን የተናገሩት የኤክስፖው ተሳታፊ ቴክኖ ሰርቪስ የተባለ የኢጣሊያ ኩባንያ ቴክኒካል ዳሬክተር ሚስተር ፍራንሲስኮ ሞራንዲ ናቸው፡፡
በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ዋጋ ርካሽ በመሆኑ በኤለክትሪክ የሚሰራ የውሃ ማሞቂያና ተጓዳኝ ምርቶችን ለማቅረብ እንዳነሳሳቸውና ይህም ሀገሪቱ የምትከተለውን አርንጓዴ ኢኮኖሚ የሚደግፍ መሆኑንም አመለክተዋል፡፡
ዳሬክተሩ እንደገለጹት ኤክስፖው የያዙትን ቴክኖሎጂ ይበልጥ ከሌሎች የፋብሪካ ባለቤቶች ለማስተሳሰር ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ጠቅሟቸዋል፡፡
በሀገሪቱ ፋብሪካዎችና ግዙፍ ፕሮጀክቶች መስፋፋት የከባድ እቃ ተሸካሚ መሳሪያ ለማምረት እንደገፋፋቸው የተናገሩት ደግሞ የኪንግ ኢንጂነሪንግ ኩባንያ ባለቤት አቶ ካህሳይ ገብረእግዚአብሔር ናቸው፡፡
በፋብሪካዎች፣ በኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድቦች የሚተከልና እስከ 500 ቶን የመሸከም አቅም ያለው የከባድ እቃ ተሸካሚ መሳሪያው የሚያነሳ ቴክኖሎጂ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ማምረት መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡
የከባድ እቃ ተሸካሚ መሳሪያው በሀገር ውስጥ መመረት መጀመሩ ጊዜና የውጭ ምንዘሪ መቆጠብ እንደሚያስችልም ተናግረዋል፡፡
የከባድ እቃ ተሸካሚ መሳሪያ ማምረቻ በአፍሪካ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ እንደሚገኝ የተናገሩት አቶ ካህሳይ ምርታቸው ወደ ምስራቅ አፍሪካ ለማቅረብ ከጀርመንና ህንድ ባለሀብቶች ትስስር ፈጥረው ለመስራት ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡
አገልግሎት ላይ የዋሉ የዘይትና የእሽግ ውሀ መያዣ ፕላስቲኮችን እንደገና በማቅለጥ የተለያዩ የፕላስቲክ ምርቶችን ማምረት መጀመራቸውን የገለጹት ደግሞ በአድዋ ከተማ የሚገኘው የፕላስቲክ ማምረቻ ፋብሪካ ተወካይ አቶ ኮኮብ ተክላይ ናቸው፡፡
አቶ ኮኮብ እንዳሉት ፋብሪካቸው ለአልመዳ ጨርቃ ጨርቅ ለአልባሳት ማሸጊያ ፣፣ለችግኝ ማፍያና ለእቃዎች መያዣ ፌስታል በማምረት ላይ ነው፡፡
የክልሉ መንግስት ከመሬት አቅርቦት ጀምሮ ባደረገላቸው ድጋፍ ከ67 ሚሊዮን ብር በሚልቅ ወጪ ተጨማሪ የጨርቃጨርቅ ፋብሪካ በመገንባት ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
የክልሉ ርዕስ መስተዳደር አቶ አባይ ወልዱ በበኩላቸው " ተወዳዳሪ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለመገንባት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንሰራለን "ብለዋል፡፡
በኤክስፖው በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተሰማሩ የኢጣሊያ ፣ የእስራኤል፣የቱሪክ፣የህንድ፣ቻይና፣የተባበሩት አረብ ኤምሬትና የሱዳን እንዲሁም የሀገር ውስጥ ጨምሮ ከ90 በላይ ባለሀብቶች እየተሳተፉ መሆናቸውን በክልሉ የአነስትኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኤጀንሲ ሀላፊ አቶ ጥላሁን ታረቀ ገልጸዋል፡፡
" ትግራይ ውስጥ ኢንቨስት ያድርጉ’" በሚል መሪ ሃሳብ የተዘጋጀው የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዓለም አቀፍ ኤክስፖ ግንቦት 18/2009ዓ.ም የተከፈተ ሲሆን ነገ ይጠናቀቃል፡፡
ግንቦት 20/2009 /ኢዜአ/

No comments:

Post a Comment

TEKLEHAIMANOT JOCO

በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ የተነሳ የእሳት ቃጠሎ በንብረት ላይ ጉዳት አደረሰ

ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ ከኤሌክትሪክ ኃይል ጋር ተያይዞ ዛሬ በተነሳ የእሳት ቃጠሎ በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ዩኒቨርስቲው አስታወቀ። በቃጠሎው በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት እንደሌለም ተመልክቷል። የዩኒቨርስቲው ...