Saturday 3 June 2017

ወጣቱ ትውልድ በተሰማራበት ዘርፍ ውጤታማ በመሆን የሰማዕታትን ራዕይ ሊያሳካ ይገበዋል -ዶክተር ደብረጽዮን

ወጣቱ ትውልድ በተሰማራበት ዘርፍ ውጤታማ በመሆን የሰማዕታትን ራዕይ ሊያሳካ ይገበዋል -ዶክተር ደብረጽዮን

"ወጣቱ ትውልድ በተሰማራበት ዘርፍ ውጤታማ በመሆን የሰማዕታትን ራዕይ ሊያሳካ ይገበዋል" ሲሉ የህወሓት ምክትል ሊቀ መንበርና የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ አባል ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ገለጹ።
የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ የትግራይ ወጣቶች ማኅበር አባላት 26ኛው የግንቦት 20 በዓል ''እኛ ወጣቶች የጀግኖች ሰማዕታት አደራን አንረሳም'' በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ በሚሊኒየም አዳራሽ አክብረዋል።
ዶክተር ደብረጽዮን በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ፍትህ፣ ነፃነት፣ ሠላምና ዴሞክራሲ በትጥቅ ትግሉ ወቅት ታጋዮች የሕይወት መሥዋዕትነት ከፍለዋል።
ወጣቱ ትውልድ የሕዝቦች ዓላማ ከራሱ ማስቀደምን መማር እንዳለበት አመልክተው፤ "ወጣቱ ለሕዝቦች ሠላም፣ ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር መስፈን ቁርጠኛ መሆን ይጠበቅበታል" ብለዋል።
በተለይም የኪራይ ሰብሳቢነት፣ የሙስናን ተግባርና አመለካከት እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ችግሮች በመታገል የልማት ወገንተኝነቱን ሊያሳይ እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት።
በውይይት መድረኩ ከተሳታፊዎች 'የትምክህትና ጠባብ ኃይል የትግራይ ሕዝብ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ሥልጣን ተጠቃሚ ነው፤ የበላይነት አለው፤ የሚለውን የውሸት ፕሮፓጋንዳ ከመሠረቱ ለመፍታት ህወሓት ምን እየሰራ ነው?' በሚል ለተነሳው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል።
ምሁራን፣ አመራር አባላትና ፖለቲከኞች ከትግራይ ሕዝብ ጋር በአካል እንዲወያዩና እንዲጎበኙ ከማድረግ ባሻገር ፊት ለፊት "የሕዝብ ለሕዝብ የግኑኝነትና የምክክር መድረክ ሥራ ጀምረናል" ብለዋል።
ባለፈው ሳምንት የአማራ ክልል የአገር ሽማግሌዎች ትግራይ ክልል በመሄድ ትምክህተኞችና ጠባብ ኃይሎች የሁለቱን ሕዝቦች ለማለያየት የተደረገ ሴራ በማውገዝ በቀጣይ ጉዳዩን በማይከሰትበ ሁኔታ ላይ መወያየታቸውን ተናግረዋል።
በተመሳሳይ ሁኔታ የትግራይ ሽማግሌዎች ወደ ጎንደር በመሄድ ውይይት እንደሚያደርጉ ጠቁመው፤ በዚህም ችግሮችን ከመፍታት ባሻገር ወደ ኢኮኖሚያዊ ትብብርና በልማት የልምድ ልውውጥ እንደሚደረግም ዶክተር ደብረጽዮን አረጋግጠዋል።
በተመሳሳይም "ከኦሮምያና ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች ጋር የሕዝብ ለሕዝብ ውይይት ይደረጋል ነው" ያሉት።
በዚህም ሕዝቦቹ በመካከላቸው የሚናፈሰውን አሉባልታ በራሳቸው ለማረጋገጥ እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል።
26ኛው ዓመት የግንቦት ሃያ የድል በዓል "የሕዝቦች እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ያረጋገጠ ፌዴራላዊ ሥርዓት እየገነባች ያለች አገር- ኢትዮጵያ" በሚል መሪ ሀሳብ እየተከበረ ነው።
ግንቦት 19/2009 /ኢዜአ/


No comments:

Post a Comment

TEKLEHAIMANOT JOCO

በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ የተነሳ የእሳት ቃጠሎ በንብረት ላይ ጉዳት አደረሰ

ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ ከኤሌክትሪክ ኃይል ጋር ተያይዞ ዛሬ በተነሳ የእሳት ቃጠሎ በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ዩኒቨርስቲው አስታወቀ። በቃጠሎው በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት እንደሌለም ተመልክቷል። የዩኒቨርስቲው ...